ባሕር ዳር፡ መስከረም 7/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ስቴት ዩኒቨርሲቲ “አንድ ደብተር ለአንድ ተማሪ” በሚል መርሕ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 2 ሺህ 400 ተማሪዎች ድጋፍ አድርጓል።
በድጋፍ አሰጣጡ ላይ የተገኙት የአማራ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጋሻው ገብሬ በቀደመው መጠሪያው የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት የአሁኑ የአማራ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የአማራ ክልል በችግር ውስጥ ቆይቷል፤ አሁንም ከችግር የተላቀቀ አይደለም፤ ይህንን ችግር እና ስብራት ለመጠገን ሥር ነቀል ትምህርት ያስፈልገዋል ብለዋል።
ሥልጠናና ምርምር ያስፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ የአማራ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመበት ሁነኛ ነገር ሕዝቡ ከችግር የሚወጣበትን መንገድ በሳይንስ ተደግፎ ችግሮችን መፍታት፣ ሰላም እና ልማት እንዲመጣ መሥራት መኾኑን ተናግረዋል።
አንድ ተቋም ከሚመዘንባቸው ቁም ነገሮች መካከል ሰው ተኮር ኾኖ የማኅበረሰብን ችግር መፍታት መኾኑንም ጠቅሰዋል። የአማራ ስቴት ዩኒቨርሲቲም የትምህርት ቁሳቁስ የማሟላት ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች ከትምህርት ተቋማት ጋር ኾኖ በመለየት ድጋፍ አድርጓል ማድረጉን ገልጸዋል።
በድጋፉ በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙት የፈለገ ዓባይ ትምህርት ቤት፣ የዕውቀት ፋና እና የመስከረም 16 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተጠቃሚ ናቸው።