ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 21/2017 ዓ.ም የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ የሦስተኛ ቀን ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
በሦስተኛ ቀን ጉባኤው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሻሻለው የአሥፈፃሚ አካላት እንደገና ማቋቋሚያ፣ ሥልጣን እና ተግባራት መወሰኛ አዋጅን አጽድቋል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሻሻለው የአሥፈፃሚ አካላት እንደገና ማቋቋሚያ ሥልጣን እና ተግባራት መወሰኛ አዋጅን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
የተሻሻለው የአሥፈፃሚ አካላት እንደገና ማቋቋሚያ እና ሥልጣንና ተግባራት መወሰኛ አዋጅን የሕግ የበላይነት በማረጋገጥ በክልሉ ያሉትን የመልማት ፀጋዎች አውጥቶ ለመጠቀም፣ የድህነት እና የግጭት አዙሪቶች በማስቀረት የትውልዶች ጥያቄ የነበረውን ብልጽግና እውን ለማድረግ መንግሥታዊ ተቋማትን ፈትሾ እንደገና ማደራጀት ማስፈለጉን ገልጸዋል።
እንደ ክልል የተሸረሸሩ እሴቶችን፣ ወጎችን እና ባሕሎችን በመንገባት፣ ሰብራቶችን በመጠገን በሥነ ምግባር የታነጸ ሀገር ወዳድ ትውልድ የማፍራት ተልዕኮ የሚሸከም ውጤታማ ተቋማት ለመፍጠር ተቋማትን እንደገና ማደራጀት እንዳስፈለገ ተናግረዋል።
የተሻሻለው አዋጅ የነበሩትን ክፍተቶች እንደሚቀርፍ ተናግረዋል። የአንደኛው ተቋም ሥልጣን እና ተግባር ከሌላኛው ጋር የማይጋጭ ግልጽ ዓላማ ይዘው እንዲደራጁም ያስችላል ነው ያሉት።
ተግባር እና ኀላፊነታቸውን ለመውጣት በቅንጅት መሥራት እና ውጤታማነትን ማሳደግ እንዲችሉ ያደርጋል ተብሏል። ኀላፊነታቸውን ሲያጓድሉ ደግሞ ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲቻል የአሥፈፃሚ አካላትን አደረጃጀት እንደገና ማሻሻል አስፈላጊ ኾኖ ተገኝቷል ብለዋል።